በኤዶ-ሴሮፍታ-ወርቃ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ የመስክ ስራ ቅኝት ተካሄደ፡፡

በኤዶ-ሴሮፍታ-ወርቃ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ የመስክ ስራ ቅኝት ተካሄደ፡፡

ሻሼመኔ ፣ ሐምሌ 21 ቀን ፣ 2015 ዓ.ም (ኢመአ):- በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ሻሸመኔ አካባቢ የመንገድ ፕሮጀክቶች ማስተባበሪያ ጽ/ ቤት ስር ቁጥጥርና ክትትል ከሚደረግላቸው የመንገድ ግንባታ ስራዎች መካከል አንዱ በሆነው 75 ኪሎ ሜትር የኤዶ-ሴሮፍታ -ወርቃ አስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የመስክ ምልከታ ተደርጓል።

ከአጠቃላይ የፕሮጀክቱ የስራ እንቅስቃሴ 67 በመቶ የሚሆነው ስራ መገባደዱን እና ቀጣይ ተግባራትን በተያዘው እቅድ መሰረት ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን በመስክ ቅኝታችን ወቅት ተመልክተናል።
ግንባታውን እያካሄደ ያለው ሀገር በቀሉ አለማየሁ ከተማ ጠቅላላ የስራ ተቋራጭ ሲሆን ፣ የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ደግሞ ጎንድዋና ኢንጅነሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማሕበር በማከናወን ላይ ነው ።

መንገዱ ከዚህ ቀደም ደረጃውን የጠበቀ መሰረተ ልማት ያልተዘረጋበትና በጠጠር መንገድ ደረጃ ተሰርቶ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ፣ በአሁኑ ወቅት ከሚኖረዉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ አኳያ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እየተገነባ ይገኛል፡፡ የፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ 1.7 ቢልየን ብር በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ነው፡፡

በእስካሁኑ አፈፃፀም የጠጠር መፍጨትና ፣ የአፈር ቆረጣ ፣ የሰብ ቤዝ ፣ ቤዝ ኮርስና ፣ የምርጥ ጠጠር (ካፒንግ) ፣ የሰብ ቤዝ ንጣፍ ፣ የቤዝኮርስ ንጣፍ ፣ የከልቨርትና የስትራክቸርስ ግንባታ እንዲሁም 20 ኪሎ ሜትር የሚሆን የአስፋልት ንጣፍ ተከናውኗል፡፡ በሚቀጥለው 2016 በጀት ዓመት የፕሮጀክቱን ዋና ዋና ስራዎች ለማጠናቅ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአካባቢው የሚስተዋለው ከፍተኛ ዝናብ ፣ የግብዓት እጥረት ፣ የወሰን ማስከበር እና ተያያዥ ጉዳዮች ፕሮጀክቱ በታሰበው ፍጥነት ልክ እንዳይጓዝ ያደረገው ቢሆንም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ፣ የአካባቢው ህብረተሰብና ባለድርሻ አካላት በቅርበት እየሰሩ እንደሚገኙ ታውቋል።

መንገዱ በገጠር ከተማ 10 ፣ በቀበሌ ከተማ 12 ፣ በዞን ከተማ 21 እና በወረዳ ደግሞ 14 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ በመገንባት ላይ ነው፡፡
የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአካባቢው በስፋት የሚመረቱ የቡና ፣ የገብስ ፣ የስንዴ እና የድንች ምርቶችን የትራንስፖርት መስተጓጎል ሳያጋጥም ወደ ገበያ ለማውጣት ያስችላል፡፡ በዚህም ረገድ የአካባቢውን እና የአጎራባች ዞን ነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።

በተያያዘም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሻሸመኔ አካባቢ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ፅ/ቤት ግንባታውን እያከናወነ ከሚገኘው የስራ ተቋራጭ ጋር በመሆን ሐምሌ 20 ቀን ፣ 2015 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካሂዷል።

Related posts

Leave your comment Required fields are marked *